Customer Support: 0943238888

Need Help?

Your Health, Anytime Anywhere

የወንዱ ልጄ የዘር ፍሬ በቦታው የለም?

Jun 30, 2025

Dr Netsanet Mengesha,(General and Pediatric surgeon, Associate Professor of Surgery)

የወንዱ ልጄ የዘር ፍሬ በቦታው የለም?

ወንድ ልጅ በእናቱ ማህፀን እያለ ፍሬው (testis) ከሆድ ማቀፊያ ወርዶ የዘር ፍሬ ማቀፊያው (scrotum) ውስጥ በሂደት ይቀመጣል። ሂደቱ ልጁ ከተወለደም በኃላ ከ3 እስከ 4 ወር ይቀጥላል። ይህ ሂደት በተለያዩ ምክንያቶች ሊስተጓጎል ይችላል። ስለዚህ ይሄ ፍሬ ከሆድ ውስጥ ወጥቶ የፍሬ ማቀፊያው እስኪደርስ ባለው መንገድ ላይ ባንዱ ቦታ ላይ ፍሬው ሊቆም ይችላል። ያም ማለት 

  • ሆድ ውስጥ ሊቀር ይችላል
  • ማቀፊያው ጋር ሳይደርስ ግን ከሆድ ወጥቶ መሃል ላይ ሊቀር ይችላል
  • ጭራሽም ማሙቶ  ጠፍቶ ሊሆን ይቸላል

 

በህክምናው (Cryptorchidism/Undescended Testis) የሚባለው ችግር ሲሆን ባንዱ ወይም ሁለቱም ፍሬዎቹ ላይ ሊከሰት ይችላል። በዋነኝነት እንደምክንያት ሚጠቀሰው ከጊዜው ቀድሞ ልጅ መወለድ (Prematurity) ሲሆን ሌሎችም ተጠቃሽ ምክንያቶች አሉ። ልጁ ከተወለደ በኃላ ከ 3 እስከ 4 ወር እድሜው ድረስ በራሱ ሊወርድ ይችላል። ከዛ በኃላ ግን ካልወረደ በራሱ የመውረድ እድሉ አናሳ ነው። ያማለት ቀዶ ህክምና (orchiopexy) ያስፈልገዋል ማለት ነው።

ወደ ፊት ልጅ መውለድ ይቸገር ይሆን?

እስከ 1 ዓመት ከግማሽ በፊት ፍሬው ካልወረደ  እና ሁለቱም ፍሬ የተጠቃ ከሆነ አዎ ወደፊት የመውለድ ችግር ሊያመጣበት ይችላል። ነገር ግን አንዱ ፍሬ ደህና ከሆነ ይሄ ችግር እምብዛም ነው።

ህክምናው ምንድነው?

ህክምናው በተቻለ መጠን ከ2 ዓመቱ በፊት በኦፕራሲዮን ፍሬውን አውርዶ ቦታው ማስቀመጥ ሲሆን፣ አንድ ወይም በሁለት ዙር ኦፕራሲዮን ሊሰራ ይችላል። 

  • ቀለል ባለ በካሜራ በታገዘ (Laparascopy) ወይም 
  • በቀዶ ህክምና (Open Orchiopexy)
  • በጣም የሳሳና የሟሟ ፍሬ ከሆነ አንደኛውን ማውጣት

 

ህክምና ካደረገስ በኃላ ሊፈጠር የሚችል የጎንዮሽ ጉዳት አለው?

  • ከማደንዘዣ ሪስክ ውጪ ኦፕራሲዮን ያደረገ ሰሞን ህመም ይኖረዋል
  • ያብጣል፣ሊደማ ይችላል
  • ቆየት ብሎ በኃላ ላይም ፍሬዋ ልትሳሳ ትችላለች
  • ተመልሶ ፍሬው ወደነበረበት ሊመለስ ይችላል

 

ከላይ  የተጠቀሱት የጎንዮሽ ጉዳቶች፣ የመከሰት እድላቸው አናሳ ነው።  

ቀዶ ህክምና ባይደረግለት ፍሬውን ሊጎዳው ይችላል? አዎ

  • ፍሬው ያለቦታው በመቀመጡና ሆድ ውስጥ በመሆኑ፣ ለከፍተኛ  ሙቀት ስለሚጋለጥ ፍሬው ከጥቅም ውጪ ይሆናል።
  • ረጅም ጊዜ ሆድ ውስጥ የቆየው ፍሬ የካንሰር የማሳደግም እድል ይኖረዋል።

 
ከህክምናው በኃላ ወላጅ ቤት ውስጥ ሊያደርግለት የሚችለው እንክብካቤ ምንድነው?

  • ኦፕራሲዮን ከተደረገለት እስከ 2 ሳምንት ቤት ውስጥ እረፍት እንዲያደርግ ማድረግ
  • የታዘዘለትን መድሃኒት ባግባቡ መስጠት
  • ሩጫ፡ ዝላይ፡ ጂምናስቲክ እንዲቀንሰ ማድረግ
  • በኃላ ላይም ልጁ ነፍስ አውቆ ራሱን ቼክ እስከሚያደርግ ድረስ ወላጅ  የልጁ ፍሬ ውስጥ አዲስ እብጠት ካለ ፣ አዲስ ህመም ካለ፣ መጠጠር ካለ ቼክ ማረግና አዲስ ነገር ካለ ልጅን ይዞ ወደህክምና መመለስ ያስፈልጋል።

 

ዋናው ነገር 

  • ወላጆች የልጆቻችሁን ዳይፐር ስትቀይሩ ፍሬዎቹ በቦታው መኖራቸውን ቼክ ማድረግ እንዳትረሱ።
  • ቀዶህክምና ለማስደረግ እስኪረፍድ አትጠብቁ

SHARE WITH